Gumii Paarlaamaa Oromoo (GPO)

Oromo Parliamentarians Council (OPC)

 

Baga Nagaan Dhuftan!Welcome to Oromo parliamentarians council!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

              New Page 2 home                         

ያልተሸፋፈነው የፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ አስገራሚ ንግግር,

 

"ለስም ወንበር ላይ መቀመጥ ዋጋ የለውም ! "

"ዛሬ 27 ዓመት በኃላ በምንም መመዘኛ ደርግ ይህን አድርጓል /ስላሴ ይህን አድርጓል እኛ ይሄን አድርገንልሃል ብለን የምንነግድበት ሸቀጥ በእጃችን የለም፡፡ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ህዝብ እንደሚያስተዳድር ድርጅት፤ ራሳችንን የምናይ ከሆነ እንደምሣሌ የሚታዩ ሀገሮች 30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለምሳሌ የኤዥያ አገሮችን ብንወስድ ዛሬ በአለም ላይ በዕድገት የሰማይ ጥግ የደረሱ አገሮች ታሪካቸው 20 30 40 ዓመታት ዕድሜ ነው፡፡ ሌላ ታሪክ የላቸውም፡፡ በዚህ ነው ራሳችንን መመዘን ያለብን እንጂ ወደኋላ ተመልሰን ሞቶ አፈር ከለበሰው ጋር ራሳችንን ዝቅ አድርገን ማወዳደር፣ በዚያ ራሳችንን ማሞኘት ይሆናል ፡፡ ከዚህ ተነስተን ስናይ መስራት ያለብን፤ መድረስ ያለብን ደረጃ ደርሰናል ወይ ብላችሁ ለጠየቃችሁ... አልደረስንም፡፡ አልደረስንም ሣይሆን ትንሽ ነገር ነው የሰራነው ብዙ ነገር ይቀረናል ብለን ራሳችንን መመዘን አለብን፡፡ ብዙ ነገር ይቀረናል፡፡ ለምንድነው እዝያ መድረስ ያቃታን መሮጥ፣ መሄድ ሲገባን ለምን አዘገምን ብዙ ችግር ስላለብን ነው፡፡ ያንን በተሃድሶአችን ደጋግመን ስላየን አልደግመውም፡፡ እንናገራለን እንጂ የምንናገረው ነገር በሽታው ያለበት ሥፍራ የሚያክም አይደለም፣ በሽታው ያለበትን ሥፍራ የሚያድን አልነበረም፡፡"

"እርግጥ ነው ንግግራችን ትልቅ ነው፡፡ ከይቅርታ ጋር ምላሳችንን አርዝመን ብዙ ተናግረናል፡፡ የምላሳችንን ያህል እጃችን ሊደርስ አልቻለም፡፡ የችግሩን ሥፍራ አላየንም አልነካንም፣ አልወጋንም፤ እንጂ እራሳችንን ማየት ቀርቶብን አይደለም፡፡ እርስ በርስ መገማገም ተጨካክነን እርምጃም መውሰድ ቀርቶብን አይደለም፤ መውጋት ያለብንን ሥፍራ ግን አልወጋንም፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ ስራችን ጎዶሎ የሆነው፡፡

መንገድ ላይ የቀረነው ብዙዎቻችን ነን፡፡ ትላንት ያሰብነው ለህዝብ ተቆርቋሪነት አጥተን ረስተን መንገድ ላይ ጥለን ያለፍን አውላላ ሜዳ ላይ የቆምን ብዙዎቻችን ነን፡፡

አንዳንዱ የራሱን ጌታ ፈጥሮ የሚሰግድለት አለ፡፡ ጌታ መፍጠር ለምን ይመጣል? ለምን አስፈለገ? ለምን ተፈለገ?.... ለሰላም ? የድርጅታችን መስመር ይህን ስለሚል? ህዝቡ ይሄን ስለሚፈልግ ???....... አይደለም፡፡ በእርግጥ የድርጅታችን ችግር ነበር ወይ ? አዎን የድርጅታችን ችግር ነበር እውነት ነው፡፡ አንድ የሚያመን ሥፍራ እዚህ ጋር ነበር መደባበቅ ስለሌለብን ነው፡፡ ለምንድን ነው ተመልሰን እርስ በርስ የምንባላው? አንድ ህዝብ ነው ያለን፣ አንድ ሀገር ነው ያለን፣ አንድ አላማ ነው ያለን፡፡ ይህ ከሆነ ለምን እንከፋፈላለን? ለምን እንባላለን? ለምን ደባና ሸር አንደኛችን በሌላኛችን ላይ እንፈፅማለን?" ምክንያቱ ግልጽ ነው "የህዝባችን ችግር ሳይሆን የግል ጥቅምን የማስቀደም ችግር ስላለ ነው፡፡ ከህዝብና ከሀገር ጥቅም የግል ጥቅምን ማስቀደም ስላለ ነው፡፡ ሌላ አይደለም ! ሌላ ፍች የለውም ! ራስን ማስቀደም ስላለ ነው:: የራስ ጌታ ሲፈጥር ደግሞ በሄደበት ሁሉ ጉልበቱ ይብረከረካል፡፡

ወንበር ላይ መቀመጥ እንፈልጋለን ወንበር ላይ መቀመጥ ለስም መሆን የለበትም፡፡ በተቀመጥንበት ወንበር ላይ ወንበሩ የሚፈልገውን ሥራ መስራት ካልቻልን ወንበሩ የሚፈልገውን ውሳኔ መስጠት ካልቻልን ለስም ወንበር ላይ መቀመጥ ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት ችግሮች ስላሉብን ነው 27 ዓመት በኋላም መድረስ የሚገባን ሥፍራ ሳንደርስ ታግለን ከታገልንለት ህዝብ ጋር የተቃቃርነው ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተጨካከነው ሌላ አይደለም አሁንም ህዝቡ የመጨረሻ እድል ሰጥቶናል በእውነት ሁሉ ነገር ድኗል ሁሉ ነገር ምላሽ አግኝቷል ሁሉ ነገር አልቆለታል ብለን የምናስብ ከሆነ ሞኝነት ነው፡፡
ራሳችንን ማሞኘት የለብንም ሀገር ሰላም ነው አዎ ሀገር ሰላም ነው፡፡ ግን ሰላም አይደለም፡፡ አጭር ዕድል ነው የሰጠን እንጂ ህዝቡ ሰላም አይደለም፣ እድል ሰጥቶናል የመጨረሻ ዕድል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚሰሩ እንይ ብሎ እድል ሰጥቶናል፡፡ ይህን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በደንብ ማጤን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡"

"እንደ ድርጅት፣እንደ መንግስት እያንዳንዳችን ከገባንበት ጓዳ ውስጥ አንገታችንን ይዞ አውጥቶ የፈለገውን ነገር ሊፈጽምብን እንደሚችል እንዲህ አይነት እርምጃ ሊወስድብን እንሚችል አይተናል፡፡በፊልም ሣይሆን በተጨባጭ ውስጥ ኖረን አይተናል ይሄ ቲያትር አይደለም፡፡ ጎበዝ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡

ወዲያና ወዲህ የምናይ ሰዎች ካለን ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ የእኛ ጌታ ህዝባችን ነው፡፡ ለየክልላችን ህዝብ ነው፡፡ ሌላ ጌታ የለንም፡፡ ለሌላ ጌታ መስገድ የለብንም፡፡ ትልቅ ድርጅት አለን 4 ሚሊየን አባላት አሉን፡፡ አራት ሚሊየን ማለት በጣም ትልቅ ነው፡፡ በአለም ላይ አራት ሚሊዬን አባላት ያሉት ድርጅት ውስን ነው፡ እንደነ ቻይና ያሉት ካልሆነ በስተቀር ውስን ነው፡፡ በቁጥር አይደለም እንዲሁ በስም ብንናገር 50 ሚሊየን ህዝብ ነው እኮ ያለን፡፡ ይህን ይዘን ለምን እግራችን ብርክርክ እንደሚል ለምን እንደምንፈራ ለምን ወደ ጓዳ ተመልሰን አንገታችንን ደፍተን እንደምናጉረመርም አይገባኝም፡፡"

"አሁን ያለን ምርጫ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ደጋግመን ስንል እንደነበረው ማዳመጥ ያለብን ማየት ያለብን ይሄንን ህዝብ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ሌላ አራማራጭ የለውም፡፡ እንደ ሥራው ክብደትና ድካም እያንዳንዱ ተቀብሎ ይሞክር ብለን አስረክበን ብንወጣም ደስ ይለን ነበር፡ ዛሬ እንደዚህ አይነት ምርጫ አለን? እስቲ ይቅርብን ሌሎችም ይሞክሩት፡፡ ሰባት አመት ሣይሆን 27 ዓመት የለፋንበት ስለሆነ፡፡ አንዳዶችን እንዲያውም ሰውነታችን የዛለ በመሆኑ ፡፡ ሌላው እስኪ ይየው ብለን እንደዚህ መቀባበል ቢቻል እንላለን፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጀ ነገር ቢኖር ደስ ባለን ነበር፡፡ እውን በዚህ ደረጃ ይህ አለ ወይ ብለን ብንጠይቅ የለም፡፡ ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡ እኛም ደግሞ መሆን ያለብንን ሳንሆን ቀርተን እየተዉረገረግን በመሄድ፣እንዲሁ አስመስለን በመጓዝ ብቻ ረጅም መንገድ መሄድ እንችላለን ወይ ብለን ብንጠይቅ አንችልም፡፡መስቀለኛ መንገድ ላይ ነዉ ያለነዉ፣ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ልናጠፋ ስለምንችል፡፡ ሀገርንም ልናፈርስ እንችላለን፡፡ ሀገር እንደ ድንገት ሲፈርስ ደግሞ አይተናል ሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤት ሀገር፡፡ በዕቅድ የሚፈርስ ሀገር የለም፡፡ ስለዚህ ያለን ምርጫ ቆም ብለን አሁንም ደጋግመን ስንል እንደነበረው ጥርሣችንን ነክሰን ከዚህ ህዝብ ጋር ሆነን ለህዝቡ መሥራት ነው ሊያዋጣን የሚችለዉ፡፡

የኦሮሚያ // ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በኦህዴድ 27 የምስረታ በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ

 

 

                                                              Copyright ©2008 GPO/OPC Allrights Reserved