Gumii Paarlaamaa Oromoo (GPO)

Oromo Parliamentarians Council (OPC)

 

Baga Nagaan Dhuftan!Welcome to Oromo parliamentarians council!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

              New Page 2 home                         

ኦሮሚኛ ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋ!

ለፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ የተሰጠ መልስ

ባይሳ ዋቅ-ወያ ****

የቋንቋዎች ትምህርት አስፈላጊነትበሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ ገጽ ላይ ያሰፈሩትን የግል አስተያየት ካነበብኩ በኋላ፣ ኦሮምኛን ሁለተኛ የፌዴራሉ የመሥርያ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ ባግባቡ የተረዱት ስላልመሰለኝ፣ በበኩሌ በሳይንስ ጥናት የተደገፈ መረጃ ባይኖረኝም እንደ አንድ ኦሮሞ ግለሰብ እስከ ዛሬ ካየሁትና ከሰማሁት እንዲሁም በልምድ በቀሰምኳቸው ዕውኔታዎች ላይ ተመርኩዤ የግሌን አስተያየት ለመሰንዘር ፈለግሁ። የፕሮፌሰርን ጽሁፍ ባንድ ጭብጥ ለማስቀመጥ ስሞክር የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አገኝበታለሁ፣

) “አንድ ቋንቋ በሃገር ደረጃ የመገናኛ ቋንቋ የሚሆንበት የራሱ ተፈጥሮያዊ መንገድ ስላለው በዚያ መንገድ ያልመጣ ቋንቋ የተጨማሪነት ዕድል የለውምይላሉ ፕሮፌሰር። ከሞላ ጎደል ትክክለኛ አባባል ነው።ተፈጥሮያዊየሚለውን ቃልመለኮታዊከሚለው ጋር ሊያማቱ የሚሞክሩ አንዳንድ ሾቪኒስቶች ሊኖሩ ስለሚችሉየራሱ ሂደትበሚል አባባል ብንተካው የተሻለ ይመስለኛል። አንዳንድ ግለሰቦች አማርኛ በፊውዳሉ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 85 በላይ ቋንቋዎች መሃል፣ የኢትዮጵያ ብቸኛ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን መደረጉን በመንግሥት ውሳኔ ሳይሆንመሆን ነበረበትብሎተፈጥሮየወሰነብን አድርገው የሚያዩ አሉና። በኔ ግምት አማርኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ የሆነው በተፈጥሮያዊ ሂደት አልነበረም አይደለምም።

ያለፈው ታሪካችን የሚያሳየን፣ በተለያዩ ጊዜያት ከሰሜንና ከደቡብ ምሥራቅ የተነሱ ተስፋፊ ኃይላት፣ ካስገበሯቸው ህዝቦች ጋር ሙሉ በሙሉ ተዋህዶና ተቀላቅሎ አንድ ወጥ ህዝብና ቋንቋ እንዲወጣ ለማድረግ አለመቻላቸውን ነው። የማድረግ አጋጣሚው እየነበራቸው ግን ለምን ሳያደርጉት እንደቀረ በትክክል ለመገምገም ሳይንሳዊ ጥናት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ካንዳንድ ገጠመኞች ተነስቼ ግን፣ ለምሳሌ አማርኛ ቋንቋ ለምን ህዝቦች በፈቃዳቸው ወድደው የሚማሩት አገር አቀፍ ቋንቋ ሳይሆን እንደቀረ ስገምተው፣ በጊዜው የነበሩ አማርኛ ተናጋሪ የመንግሥት አስተዳዳሪዎችም ሆኑ የአብያተ ክርስቲያናት አባዎች፣ ቋንቋውን በጣም ከማፍቀራቸው የተነሳተሸናፊ ብሄሮችበሰፊው ከለመዱት የሚረክስ መስሎ ስለታያቸው ይመስለኛል። 1940 ዎቹ መጀመርያ ላይ የወለጋ ገዢ የነበሩ ደጃዝማች መኮንን ደስታ፣ ጠቅላይ ግዛቱን እየዞረ ሲጎበኝ፣ በግዕዝ ፊደል የተጻፈው ኦሮሚኛ መጽሃፍ ቅዱስና መንፈሳዊ መዝሙሮች በጠቅላይ ግዛቱ መስፋፋታቸውን ከተረዳ በኋላጋልኛን ለመሳሰሉ ቋንቋዎች የግዕዝ ፊደልን መጠቀም ፊደሉን ማርከስ ነውብሎ ያወጣው መመርያ፣ ቋንቋውተፈጥሮያዊበሆነ መንገድ አድጎ አገራዊ እንዳይሆን ትልቅ ዕንቅፋት የነበሩት የቋንቋው ባለቤቶች ራሳቸው ለመሆናቸው አመላካች ይመስለኛል።

በተግባር ደግሞ ያየሁት፣ ለምሳሌ ተወልጄ ባደግሁበት ወረዳ፣ አማርኛ ቋንቋ የፍርድ ቤትና የፖሊስ እንጂ የሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋ አልነበረም። ፍርድ ቤቱም ፍትህ የማይገኝበትና ፖሊስ ጣቢያውም የእስር ቦታ በመሆኑ በነዚያ አካባቢ ብቻ የሚነገረውን አማርኛ ቋንቋን ያካባቢው ህዝብ በበጎ ዓይን አያየውም ነበር። በትምህርት ቤትም፣ ለወደፊቱ ህይወታችን የሚጠቅመን መሆኑን ተረድተን በፍላጎት የተማርነው ሳይሆን ተገድደን ስለነበር እስከዛሬም ድረስ ብዙዎች ጓደኞቼ አማርኛ ቋንቋን በበጎ ዓይን አያዩትም። አንድም አማርኛ ተናጋሪ በሌለበት ወረዳ፣ ከሁለት ሺህ ተማሪ ውስጥ አንድም አማርኛ ተናጋሪ በሌለበት /ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ አማርኛ ብቻ እንድናወራና ኦሮሚኛ በተናገርን ቁጥር እየተቀጣን ማደጋችን፣ ቋንቋውን ወድደን እንዳንቀበለው አድርጎናል። ለዚህ ነው አማርኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ የሆነው በመንግሥት ግፊት እንጂ ፕሮፌሰር እንደሚሉትተፈጥሮያዊ መንገድን ተከትሎአይደለም ብዬ የምሞግተው። መንግሥት ደግሞ እጁን ማስገባት ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንዲተረጎም ህገ ደንቦችን አውጥቶ ሥራ ላይ በማዋሉ፣ ለምሳሌ አማርኛን በደንብ ባለማወቅ ብቻ ዩኒቬርሲቲ ለመግባት ያልቻሉ ኦሮሞዎች ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም።

) ፕሮፈሰርቋንቋ በመማር የመንግሥት እጅ ከገባበት እጅ እጅ ይላልያሉት መቶ በመቶ ልክ ነው። እሳቸው እንኳ ለማለት የፈለጉት አሁን ኦህዴድኦሮምኛ ሁለተኛ የፌዴራሉ የመስርያ ቋንቋ ይሁንብሎ በመጠየቁና ኦህዴድ ደግሞመንግሥትስለሆነ፣በቋንቋ መማር ውስጥ እጁ መግባት የለበትምማለታቸው መሰለኝ። በመቀጠል የተናገሩት ግን የመልዕክታቸውን ዕውነተኛ ገጽታ ያሳያል፥ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣይሉናል ፕሮፌሰር፣

ብሄራዊ ቋንቋ መሆኑን አማርኛ ቀደም ብሎ ወስዶታል። ዛሬ ከእንግሊዝኛ በቀር የሚያሰጋው ቋንቋ የለም። ግፋ ቢል፥የኛም ቋንቋ በመንግሥት ደረጃ ተጨማሪ መጠቀሚያ ይሁንየሚሉ ሊቲከኞች ቢነሱ ነው። ይህን ዓይነት ጥያቄ ማስተናገድ ደግሞ ከታሪካዊ ሂደት ወጥቶ ህዝብ ላይ ከባድ ጫና በግድ መጫን እንጂ፣ ባይማሩት ቢቀር የማይጎድ ቋንቋ ለማስተማር በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ቋንቋ የመገናኛ መሳርያ ከሆነ ሁለተኛ ቋንቋ መማርና ማስተማር ጊዜና ሃብት ማባከን ነውበማለት ጥያቄውን ያጣጥላሉ። (ስርዝ የኔ)

በነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ብዙ የተለያዩ፣ ግን ደግሞ የተያያዙ ሃሳቦች ተካትተዋል። በሳቸው ግምት እንግዲህ አማርኛየመንግሥት እጅ ሳይገባበትእናተፈጥሮያዊበሆነ መንገድ ከሁሉም ቀድሞ አስተማማኝ ቦታ ስለያዘ የሱን ቦታ የሚቀናቀነው ወይም የሚያሰጋው ሌላ ቋንቋ የለም። በአማርኛ የብሄራዊ ቋንቋ መሆን በመንግሥት ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በህግም የተደነገገ ስለሆነና አስቀድሞ ቦታውን የያዘውም ታሪካዊ የቋንቋዎችንና የብሄሮችን በርስ በርስ የመቅለጥ ተፈጥሮያዊ ሂደት ተከትሎ ነው አይደለም በማለት ጊዜ ማጥፋት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። የማያጣላን እውኔታ ግን ዛሬ፣ አማርኛ ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሁሉ ይበልጥ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮች መግባቢያ ቋንቋ ነው። በሥነ ጽሁፍ ደረጃም፣ ምንም እንኳ ይሰጠው ከነበረው የመንግሥት ድጋፍና አንጻር የተጠበቀበትን ያህል ለማደግ ባይችልም ዛሬ ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተሻለ መልኩ ዳብሯል ማለት ይቻላል። ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለማሳደግ በህግም በልምድም በተከለከሉበትና የብሄር ጭቆና በተንሰራፋበት የፊውዳሉ ዘመን የሥራ ውጤት ነው። ዛሬ ግን ይህን ውይይት የምናካሄደው በፌዴራል ኢትዮጵያ ዘመን ነውና፣ ስለቋንቋዎች እኩልነት ያለን አስተሳሰብ መቀየር ያለበት ይመስለኛል። በንጉሡ ዘመን ተገድደው አማርኛ ብቻ እንዲማሩ የተደረጉ ኦሮሞዎች ዛሬ በክልላቸው ውስጥ በገዛ ቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ ብቻ ሳይሆን የማሳደግንም ዕድል አግኝተዋል። በህዝብ ቁጥር ብዛት ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች ሁሉ የላቁ በመሆናቸው፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ እኩል የፌዴራሉ የመስርያ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቃቸው የሚያከራክር ጉዳይ መሆ አልነበረበትም። ይህከአማርኛ እኩል የፌዴራሉ የመሥርያ ቋንቋ እንዲሆንብለው የጠየቁትን የእኩልነት ጥያቄ ነው እንግዲህ ፕሮፌሰርን ትንሽ ያሳሰባቸው። ኦህዴድ የጠየቀው እኮከአማርኛ እኩልእንጂአማርኛን ተክቶየሚል ስላይደለ ያናደዳቸው ምኑ ላይ እንደሆነ ባይገባኝም፣ ለማሳመን ብለው ከላይ በሰፊው በጠቀስኩት የጽሁፋቸው ቁራጭ ውስጥ ያሰፈሩት ምክንያቶቻቸው ግን ብዙም ውሃ የማይቋጥሩ ሆነው ነው ያገኘኋቸው።

በመጀመርያ ደረጃ ኦሮምኛን የፌዴራሉ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እየጠየቀ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ እንጂ እሳቸው እንዳሉትየኛም ቋንቋ ከአማርኛ እኩል ተጨማሪ ያገሪቷ መስርያ ቋንቋ ይሁን ብለው በሚደፍሩ ፖሊቲከኞችአይደለም። ባይማሩት ቢቀር የማይጎድ ቋንቋ የምትለዋ ግን ትንሽ የሾቪኒስትነት ጠብታ ያለባት መሰለኝ። ፕሮፌሰር እንደ አንድ ምሁር፣ የሰው ልጆች ማንነት መገለጫዎች ከሆኑት አንዱ የሆነውን ያንድን ህዝብ ቋንቋሳይማሩ ቢቀር የማይጎዳበመሆኑ በሱ ላይ ጊዜና ሃብትን ማባከን አያስፈልግም ብለው ብደ ፍረት ሲናገሩ፣ በቋንቋ እኩልነት የማያምኑ ግለሰብ ናቸው ብሎ ማለፉ የሚሻል ይመስለኛል። ወያኔ በመሳርያ ትግል ብርታት ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች ቀድሞ አራት ኪሎ ደርሶ ዙፋን ላይ መቀመጡ ሂደቱንየአጋጣሚእንጂየተፈጥሮአዊየማያደርገውን ያህል የአማርኛ ቋንቋም በመንግሥት ሙሉ ድጋፍከሁሉም ቀድሞብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን መደረጉ ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሻለ አያደርገውም። ይህባይማሩትም ቢቀር የማይጎዳየሚለው አባባል ግን ትንሽ የሾቪኒስትነት ጠብታ ስላላት፣ ታዝቦ መተው ነው እንጂ በሱ ላይ ጊዜ ማባከኑ አስፈላጊ አይመስለኝም። እንደሁ ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ግን፣ ማንኛውንም ቋንቋ የመማር ዕድሉ እያለ ሳይማሩት ቢቀር እጅግ በጣም ጎጂ ነው። ቋንቋን አለማወቅ ግን ባይታወር ያደርጋል፣ ዕውቀትን ይገድባል፣ ከሰው ልጆች ጋር ተግባብቶ በሰላም የመኖርን ዕድል ያጠባል። ቋንቋን ማወቅ ዕውቀት ያዳብራል፣ ስለ ዓለምን ስለ ህዝቦች ያለንን አመለካከት ያሰፋል። እኔም ይሄው ባማርኛ ቋንቋ ከፕሮፈሰር ጋር ሙግት የምገጥመው አማርኛን ስለተማርኩ ነው። እሳቸው ግን በኦሮምኛ ቋንቋ ሊሞግቱኝ የሚችሉ አይመስለኝም። ስለዚህ ውድ ፕፌሰር፣ ሳይማሩት ቢቀር የማይጎዳ ቋንቋ የለም ማለቴ ነው።

ሁለተኛ ቋንቋን መማር ጊዜና ሃብትን ማጥፋት ነውይላሉ ፕሮፌሰር ለኢትዮጵያ ህዝቦችጊዜና” “ሃብትብክነት ተቆርቁረው። አዎ! እንደ አንድ ዜጋ የኢትዮጵያ ህዝብ አጥሮት እየተቸገረ ካለው ወርቃማ ጊዜ ቆርሶ ኦሮሚኛን በመማር እንዲቃጠል ማድረግኃላፊነት የጎደለውመሆኑን ማስገንዘባቸውና፣ አገሪቱ የተቆለለባትን ዓለም ዓቀፋዊ ዕዳ መክፈል አቅቷት በመጨነቅ እያለች፣በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍእንዲሉ፣ ኦሮሚኛን ለማስተማር በጀት መመደብ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡ ይመስላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ተጨማሪ ቋንቋ የመማርያ ጊዜም ገንዘብም የለውም ነው የሚሉን። ፕሮፌሰር ግን ያልተረዱት ነገር ቢኖር፣ ኦሮሞዎች ቋንቋቸው ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን ማለት የማንነትና የእኩልነት መብት ጥያቄ መሆኑን ነው። እንደ ኢትዮጵያውነታቸውና ወደ አርባ በመቶ የሚጠጋ ህዝብ ሆነው፣ ቋንቋቸው ተጨማሪ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እየጠየቁ ነው። መጠየቅም መብታቸው ነው። ኦሮሚኛ ደግሞ ሌላው የፌዴራል ቋንቋ ቢሆን የአገሪቱን ህዝብ ወርቃማ ጊዜም ሆነ ሃብት ለብክነት አይዳርግም። ለጥያቄው አጥጋቢ መልስ እስኪገኝ ግን ኦሮሞዎች ድምጻቸውን ለማሰማት ትምህርት ቤት እየዘጉና የሥራ ማቆም ዓድማ እያወጁ በየአደባዩ መውጣቱን ይቀጥላሉ፣ ያኔ ነው እንግዲህ ፕሮፈሰር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቃማ ጊዜና ሃብት መባከን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል የሚረዱት።

) ሌላው ፕሮፌሰርን ያሳሰባቸው ነገር ደግሞለመገናኛ የማያስፈልግ ቋንቋን ተናጋሪዎችን ብቻ ለማስደሰትመማር ወይም ማስተማርን ነው። ፕሮፌሰር ከምን አንጻር እንደተመለከቱት አይታወቅም እንጂ፣ ለመገናኛ የማያስፈልግ ቋንቋ በምድራችን ላይ የለም። ምናልባት ፕሮፌሰር ለማለት የፈለጉት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሚኛለመገናኛ የማይስፈልግ ቋንቋ ስለሆነከአማርኛ ጎን የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ መሰለፍ የለበትም ከሆነ፣ መልሱ ተሳስተዋል ነው። ምናልባት ከአማርኛ እኩል በሁሉም 3 | P a g e ክልሎች የመግባቢያ ቋንቋ አይሆን እንደሁ እንጂ፣ ኦሮሚኛ በብዙ የኢትዮጵያ ብሄሮች መካከል የመግባቢ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ነው። ከዚያም በላይ የኦሮሚያ ክልል በቆዳ ሰፋትና በህዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ ለሚመረቱት አላቂና ዘላቂ ሸቀጦች ትልቁን ተጠቃሚ ገበያተኛና ገበያ አቅራቢ ስለሆነ፣ ሸቀጦቻቸውን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለመሸጥ ወይም ሠርተው ለማደር ለሚፈልጉ የሌላ ብሄር ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች የኦሮሚኛን ቋንቋ በመጠኑም ቢሆን ማወቅ ለኑሮአቸው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ልጅ ሆኜ ባደግሁባት ትንሽ ከተማ ውስጥ በየቅዳሜው የባህል ልብስ ለመሸጥ ይመጡ የነበሩ ጉራጌዎች ገበያተኛ ለመሳብግፍቲ ኩኒ ቀሚሲ ጋሪዳ ድር በድሪዳ ህን ሃላቁወዘተ እያሉ የሚያውቋትን ሶስት ዓረፍተ ነገር ጮክ እያሉ ያለመታከት ይለፍፉ የነበሩት፣ በኦሮሚኛ ከተናገሩ ጥሩ ገበያ እንደሚያገኙ ጠንቅቀው ስላወቁ ነበር። ስለዚህ፣ አንደኛ፣ ለመገናኛ የማያስፈልግ ቋንቋ የለም፣ ሁለተኛ፣ የሰው ልጅ አንድን ቋንቋ የሚማረውና የሚያወራው ለራሱ ጥቅም ብሎ እንጂ ተናጋሪውን ህዝብ ለማስደሰት አይደለም። እኔም አማርኛን የማወራውና የምጽፈው፣ ያቀድኩትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የጠቅመኛል ብዬ እንጂ አማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ለማስደሰት አይደለም!

) እንደማስበው ከሆነ፣ የፕሮፌሰር የተደበቀ ትልቁ ፍርሃት የመነጨው የኢትዮጵያ በክልል መከፋፈልና፣ ክልሎችም ከፈለጉ የየራሳቸውን ቋንቋ የክልላቸው የመሥርያ ቋንቋ ማድረግ ከመቻላቸው የተነሳ መሰለኝ። ለዚህም ይመስለኛል፣ቋንቋ እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚቻለው መጀመርያ ክልሎችን በማፍረስና ከላሊዎችን በመደምሰስ ነውብለው ቅድመ ሁኔታ ለማስቀመጥ የደፈሩት። ፕሮፌሰር ክልልና ኬላን ያማቱ ይመስለኛል። አዎ ፌዴራላዊ አስተዳደር ባገራችን ሥራ ላይ ሲውል የመጀመርያ ጊዜ በመሆኑና ፕሮፈሰርም የተማሩት እንደኔው አማርኛ ብቻውን ብሄራዊ ቋንቋ በነበረበት አሃዳዊሥርዓት ዘመን ስለሆነ፣ ክልልና ኬላ ቢማታባቸው አያስገርምም። ግን ከዚህ የፕሮፌሰር ዓረፍተ ነገር የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ እሳቸውን ያስቆጣቸውየኦሮሚኛ ቋንቋው መስፋፋትብቻ ሳይሆን ያገሪቷ በክልል መከፋፈሏም ጭምር ነው። በሳቸው ምክር መሰረት፣ ኦሮሚኛ ቋንቋ እንዲስፋፋ ከፈለግን በመጀመርያ ደረጃ ክልሎችን ማፍረስ፣ ቀጥሎ ደግሞከላሊዎችን መደምሰስአለብን ማለት ነው። ለመስማትም የሚከብድ ሥር ነቀል እርምጃ! ማፍረስና መደምሰስ!

) የፕሮፌሰር ፍርሃት ባገሪቷ በክልል መከፋፈል ላይ ብቻ አልተወሰነም። አማርኛ ቦታውን ቀድሞ በመያዝ ብሄራዊ ቋንቋ በመሆኑ፣ኦሮምኛን መላ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲማሩት በበቂ ምክንያት ከተወሰነ፥ ልጆቹ በለመዱት፣ በተፈተነው፣ በቆንጆው የኢትዮጵያ ፊደል መጻፍ አለበትይሉናል። ፕሮፌሰር በእጅ አዙር እየነገሩን ያለው፣ ኦሮሚኛ እንደው ባጋጣሚ መላ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲማሩትከተወሰነባቸው በግድ በሳባውያን ፊደል መጻፍ አለበት ማለታቸው ነው። ይህንን የሳቸውን የጸረ-ቁቤ አቋም ከዚህ በፊትየቁቤ ጉዳይ ሳይቸግር ለቸገራቸውበሚል የውይይት መነሻ ጽሁፌ በጥልቅ የመረመርኩት ስለሆነ አሁን ባልመለስበትም፣ በድጋሚ የሚከተለውን ለማለት እሻለሁ። መደጋገም የዕወቀት እናት ነው ተብሏልና!

ለኦሮሚኛ ቋንቋ እንዲመች አሻሽለን እየተጠቀምንበት የነበረው የሳባውያን ፊደል ተስማሚነቱ ለአማርኛ እንጂ ለኦሮሚኛ ቋንቋ አለመሆኑን ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ የተወያየንበትና አንዳችን ሌላውን ለማሳመን ያልቻልንበት በመሆኑ ላለመስማማት ተስማምተን ኑሮን እንግፋበት። በዚያ ከተስማማን፣ ኦሮሚኛ የፌዴራሉ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆንበበቂ ምክንያት ከተወሰነ ለሩብ ምዕት ዓመት ተፈትኖና ተስማሚ ሆኖ ያገኘነውን የላቲን ፊደል ትተን፣ አማርኛ ተናጋሪዎችን ብቻ ለማስደሰት ብለን በሳባውያን ፊደል በመጠቀም የግላችንን ደስታ የምንሰዋበት ምክንያት አይታየኝም። ከዚያም በላይ ዛሬ ባገራችን ያለው ትውልድ ሰማንያ በመቶው በክልል አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያደገ በመሆኑ፣ ያን ያህል ብዛት ያለውን የኦሮሞ ህዝብ፣ እየወደደው ሲማርበትና ሲራቀቅበት የኖረውን፣ በህዝቦች ተፈቃቅሮና አብሮ በሰላም ለመኖር ላይ ደግሞ አንዳችም ዓይነት አሉታዊ ገጽታ ያልፈጠረውን በላቲን ፊደል መጠቀምን ለማን ተብሎ፣ ተውሰነውና ሞክረነው ሳይስማማን ሲቀር በመለስነው በሳባውያን ፊደል እንደምንቀይር አይታየኝም። ሁሌም የማይገባኝ ነገር ቢኖር፣ ሲናገሩት ምንም ዓይነት አሉታዊ ጎን የሌለው የኦሮሚኛ ቋንቋ፣ በላቲን ፊደል ሲጻፍ ለምን አሳሳቢ እንደሚሆን ነው። ኦሮሞዎች እኮ ቋንቋውን መናገር የጀመሩት ጥንት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከመፈጠሯ በፊት ሲሆን፣ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያንም ደግሞ ከሌሎች ጋር ሆነው ከመሰረቷት በኋላ ለአንድም ደቂቃ ያለማቋረጥ ይኼው እስከዛሬ ድረስ እየተናገሩ ሲሆን፣ በቋንቋቸው መጠቀማቸው አንድም ጊዜ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ላለመግባባት ምክንያት ሆኖ አያውቅም። በዚህ ሁሉ ዘመን በቋንቋቸው በመናገራቸው ምንም ዓይነት ችግር ያልተፈጠረውን ያክል፣ ዛሬም ያንን ይነጋገሩበት የነበረውን ቋንቋ በላቲን ቢጽፉት ለምን ፕሮፌሰርን እንዳስቸገራቸው የማይገባኝ ነገር ነው።

መደምደምያ፣

ውድ ፕሮፌሰር፣ በዓለማችን ላይ ያሉ ከአምስት ሺህ በላይ ቋንቋዎች በጋራ የሚጠቀሙት የአሥራ አራት ቋንቋዎችን ፊደል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በምድራችን ላይ ያሉት ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ብሄር ተወላጆች ለቋንቋቸው የሚስማማውን ፊደል የመምረጥ ዕድል የተሰጣቸው፣ የሳባውያንን ፊደል ጨምሮ ከአስራ አራቱ ፊደላት ብቻ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በምድራችን ላይ የሚኖሩ ሰባት ቢሊዮን የሰው ልጆች ከአሥራ አራቱ ብሄር/ህዝብ በስተቀር፣ የሚነጋገሩባቸው ቋንቋዎች በተውሶ ፊደል የተጻፉ ናቸው ማለት ነው። በኢትዮጵያም የትግርኛና አማርኛ ተናጋሪዎች ለቋንቋቸው የሚስማማቸውን ፊደል ለመሸመት ወደ ፊደል ገበያ ሲወጡ ተስማሚ ሆኖ ያገኙትን የሳባውያን ፊደልን ነው ሸምተው የተመለሱት። የሸመቱትም ፊደል ለቋንቋቸው በጣም ተስማሚ ሆኖ ስላገኙት ይኼው እስከዛሬ ድረስ ያላንዳች ማጉረምረም እየተጠቀሙበት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ግን ወደ ቋንቋ ገበያ ወጥቶ የመረጠውን የመሸመት ዕድል ስላልነበረው የፊውዳሉ ሥርዓት የመረጠለትን የሳባውያን ፊደል ተውሶ ለሁለት ምዕተ ዓመት ከተጠቀመበት በኋላ፣ በነጻ የቋንቋ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚስማማውን የመሸመት አጋጣሚ እንዳገኘ፣ ወዲያውኑ የላቲንን ፊደል ሸምቶ መጠቀሚያ ካደረገ ይኸውና ሶስት አሥርት ዓመታት ሊሆነው ነው። እስካሁን ድረስ ተውሰን ያመጣነው የላቲን ሸቀጥ አንዳችም ዓይነት ጎጂነት የሌለውና ለቋንቋው ዕድገት በጣም ተስማሚ ሆኖ ስላገኘነው በሂደት ውስጥ ሌላ የተሻለ እስክናገኝ ድረስ እየተጠቀምንበት እንቀጥላለን። ፕሮፈሰርንም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብን ለሚያስተናግዱ ወገኖቼን ሁልጊዜም እየጠየቅሁ ግን ደግሞ መልስ ያላገኘሁለትን ጉዳይ ደግሜ ልጠይቅና፣ ኦሮሞዎች በላቲን ፊደል መጠቀም ከጀመሩ ይሄው ሰላሳ ዓመት ሊሞላው ሲሆን፣ ይህን በሚያክል ጊዜ ውስጥ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችና በኢትዮጵያ ራስዋ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን እንደሆነ ዕቅጩን ቢነግሩን ለውይይቱም የሚያመች ይመስለኛል። አለበለዚያ ግን ስንት አንገባጋቢ የሆነ ያገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ህልውናን የሚፈታተን አገራዊ ቀውስ እየተስተዋለ ባለበት ባሁኑ ሰዓት ዋናውን ችግር መጋፈጥን ፈርቶ አላስፈላጊ ወደሆነ ጥያቄ የህዝብን ቀልብ ለመሳብ መሞከር ኃላፊነት የጎደለው አቀራረብ ይመስለኛል።

በኔ ግምት፣ ስለቋንቋው አወቃቀርና አጠቃቀም አንዳችም ዕውቀት የሌላቸው ግለሰቦች ተነስተው፣ ኦሮሚኛ በዚህ ወይም በዚያኛው ፊደል መጠቀም አለበት እያሉ በምንም ሳይንሳዊ ጥናት ያለተደገፈን ነገር እንደ አገራዊ ጉዳይ አድርጎ ማቅረብ ጭፍን ሾቪኒስታዊነት ይመስለኛል። እኔ የአማርኛ ቋንቋን ሰዋሰው ጠንቅቄ ባውቅም፣ ለቋንቋው እድገትና መዳበር አማርኛ ተናጋሪውን ብሄር ወክዬ በዚህ ፊደል ይጻፍ፣ ይኸኛው የበለጠ ይስማማዋል ለማለት ግን አልደፍርም። ያማ ቢሆን ኖሮ፣ ገና አንደኛ ክፍል ስገባ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑትን የሳባውያንን ፊደል ከመሸምደድ ይልቅ ሃያ ስድስት ፊደላት ብቻ ያለውንና ለመማር በጣም የሚቀለውን የላቲንን ፊደል ለአማርኛ ጠቀሜታ እንዲውል በመከርኩ ነበር። የራስ ባልሆነ ነገር ላይ ለማዘዝ መሞከር ደግሞ የራስን መብትና ገደብ አለማወቅ ይመስለኛል። ቀኑን ሙሉ ሲያስብበትና ሲናገርበት ውሎ ሌሊቱን ደግሞ ሲያልምበት የሚያድረውን ኦሮሚኛን ቋንቋ ዋጋ እንደሌለው ቆጥሮ በአማርኛ እንዲያስብና እንዲያልም ማስገደድ በህዝቦች መሃል መከፋፈልን እንጂ መፋቀርን አያጎለብትም። ቋንቋ ደግሞ ከማንነት ጥያቄዎች የመጀመርያው በመሆኑ፣ ተናጋሪዎቹ በምንም ዓይነት በሌላ ቋንቋ ሊለውጡት ካለመፈለጋቸው የተነሳ የትም ይሁን የት፣ እንኳን ባገራቸው ይቅርና በሰው አገርም ያንን የማንነት ጥያቄ እንደተሸከሙ ነው የሚዞሩት።

በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን እንደ ፌዴራሉ የመሥርያ ቋንቋ በመጠቀም ዙርያ፣ እንደ ፕሮፌሰር ደፍረው በግልጽ አይናገሩትም እንጂ ተመሳሳይ አስተሳሰብን የሚያስተናግዱ ሌሎችም ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ደግሞ ቋንቋዎችን በእኩልነት ዓይን ካለማየት የሚመጣ ችግር ይመስለኛል። ችግር እስከሆነ ድረስ ደግሞ በቅንነት ተወያይቶ መፍትሄ መፈለግ ነው እንጂ ችግሩ እንዳልነበር ወይም እንደሌለ መቁጠር ሃላፊነት የጎደለውና ችግርን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማውረስ የተደረገ የቸልተኝነት ሥራ ይመስለኛል። በኔ ግምት፣ ችግሩ የአንዳንድ ያንጋፋው፣ በአሃዳዊ ሥርዓት ያደግንና ለብሄር ጥያቄ መፍቻው አንዱ ቁልፍ ፌዴራላዊ አስተዳደር መሆኑን ለመቀበል ያዳገተን ትውልድ ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብማ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በኦሮሞዎች የላቲን ፊደል መጠቀም ቅሬታ አላሰማም። የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ በሰላሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቋንቋውንና ሥነ ጽሁፉን አዳብሮ በታሪኩ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እየተደሰተ ነው። ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ የሳባውያንን ፊደልን ተጠቅሞ የተጻፈ አንድ የኦሮሚኛ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ሲሆን፣ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሥነ ጽሁፎችን አበርክቷል። ይህንን የኦሮሞን ህዝብ ያስደሰተውን ሂደት ነው እንግዲህ ለጥቂት ግለሰቦች ደስታ ተብሎ እንድንተወው ፕሮፌሰር የሚወተውቱን።

እስቲ ላንዳፍታ ቆም ብላችሁ አስቡ፣ የኦሮሞ ህዝብ ከዘመናት ትግል በኋላ የራሱ ክልል ኖሮት በራሱ ቋንቋ መጠቀም ከጀመረ ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ የሚሰማው ደስታ ከግምት በላይ ነው። የዚያኑ ያክል ደግሞ ከሌሎች ብሄሮች ጋር ተከባብሮ በእኩልነት የመኖሩን ሁኔታ ትልቅ ከፍታ ላይ አድርሶታል። ለምሳሌ ያህል በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች መካከል ያለው የመቀራረብና የመዋደድ ሁኔታ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታይ ደረጃ ላይ የደረሰው ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ነው። ፕሬዚዴንት ለማ መገርሳ ባህር ዳር የሄዱ ጊዜ ሊቀበላቸው የወጣውን ህዝብ ብዛትና እሳቸውም በውብ አማርኛ ያንን ህዝብ ሲያማልሉ ከማየት በላይ ለብሄሮች መቀራረብና መከባበር ተጨማሪ ዋቢ ማቅረብ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ፕሬዚዴንት ገዱም ኦሮሚያን ሊጎበኙ መጡ እንበልና፣ ልክ ፕሬዚደንት ለማ እንዳደረጉት እሳቸው ደግሞ ሊቀበላቸው የወጣውን የኦሮሞ ህዝብ በኦሮሚኛ ቢያነጋግሩ፣ ምንኛ እንደሚያስደስት መገመት አያዳግትም። እንኳን በህዝቦች መካከል ይቅርና በሁለት ያገር መሪዎች መካከል የሚደረገው ግንኙነት በአስተርጓሚ በኩልና ያለ አስተርጓሚ ሲካሄድ ውጤቱ የተለያየ ነው። ስለዚህ ነው የኢትዮጵያ 5 | P a g e ህዝቦች በተቻለ መጠን ያለ አስተርጓሚ እንዲነጋገሩ ቢደረግ ፍቅርን ያዳብራል እንጂ አያመነምንም የምለው። የኦሮሚኛ ተጨማሪ የዴዴራሉ የመሥርያ ቋንቋ ይሁን የምንለውም ከዚህ በመነሳት ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች በሙሉ የየራሳቸውን ቋንቋ በመተውቀድሞ ቦታውን የያዘውንየአማርኛ ቋንቋን በግድ እንዲማሩ ሳይሆን፣ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ተጠብቆላቸው በመከባበርና በእኩልነት እንዲኖሩ፣ ብሎም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላንዳች ገደብ ለመዘዋወርና ለመስራት እንዲችሉ ከተፈለገ ቢያንስ ቢያንስ ላብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሥራ ዕድልና የሚገኝበትና የምርቶች ገበያ የሆነችውን የኦሮሚያ ክልልን ቋንቋ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እንዲያውቀው ቢደረግ በህዝቦች መካከል ትብብርን ያጠነክራል ብዬ አምናለሁ። ማለት፣ ኤኮኖሚን ያሳድጋል፣ ብሎም አገር ታድጋለች። ትላልቅ ፋብሪካዎች ይፈጠራሉ፥ በየፋብሪካው ላይ የሚሰሩ ከተለያዩ ብሄሮች የተወጣጡ ወዝ አደሮች በሂደት ውስጥ ለመግባብያ የሚያመቻቸውን አንድ ቋንቋ መጠቀም ይጀምራሉ፣ የኤኮኖሚ ትስስሩና የህዝቦች በነጻ የመንቀሳቀስ ክስተት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል፣ ቀስ እያለ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ እንዲከበርላቸው ሲጠይቁ የነበረው ክልላዊ መብታቸው ያለክልልም እንደሚከበርላቸው እያወቁ ሲመጡ፣ ራሳቸውን ከክልል ባሻገር ማየት ይጀምራሉ፣ በሂደትም አንዳንዶች ቋንቋዎች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ ብሎም እየከሰሙ ይሄዳሉ። ህዝቡም፣ ቋንቋን ከመብትና ከማንነት ጥያቄ አንጻር ማየት ይተውና ከግል ጥቅም ጋር ብቻ ማዛመድ ይጀምራል፥ ኢትዮጵያምብሄራዊ አገርወይም በእንግሊዝኛ nation-state ልትሆን የምትችለው ይህንን ተፈጥሮያዊ ሂደት ስትከተል ብቻ ነው።

ይህ እንግዲህ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ነው። ወደ ተግባር ተተርጉሞብሄራዊ አገርእንዲመሰረት ከልባችን የምንመኝ ከሆነ ደግሞ የፕሮፌሰሩን አማርኛ ብቻምክር ወደ ጎን ትተን፣ ኦሮሚኛን ተጨማሪ የፌዴራል መስርያ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን፣ በአማራ ክልል ውስጥ ሁለተኛ የክልሉ ቋንቋ እንዲሆን፣ አማርኛም ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሁለተኛ የመማርያ ቋንቋ ማድረግ ነው። ያኔ የአማራው ዩኒቬርሲቲ ተመራቂዎች ያላንዳች ገደብ በኦሮሚያ፣ ኦሮሞ ተመራቂዎች ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ፣ ዛሬ በቋንቋ አለመቻል ምክንያት ዕውን ሊሆን ያልቻለው ተጨማሪ የሥራ ገበያ ተከፈተላቸው ማለት ነው። ተከባብሮ ተፈቃቅሮና በእኩልነት አብሮ ለመኖር ችግር እስካልፈጠረ ድረስ ደግሞ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች ያገሪቷ የመሥርያ ቋንቋ ቢሆኑ ችግር ሊኖረው አይገባም። ለዚህም ነው ባገራችን፣ ኦሮሚኛ ብቻ ሳይሆን ትግርኛም የፌዴራሉ መሥርያ ቋንቋ ቢሆን ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም የምለው። ፕሮፌሰርምአማርኛ ቀድሞ ቦታውን ስለያዘ ሌላ ተቀናቃኝ አያስፈልገውምየሚለውን ልዩነትን የሚያሰፋ እንጂ የማያጠብ አስተሳሰባቸውን ትተው ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ቢያስተካክሉ የሚሻል ይመስለኛል። ህብረተሰብ፣ የተወሰነ የጋቢና መቀመጫ ብቻ የተሰራለት የኦቦ አቦሴ ቶዮታ ሳይሆን፣ ቀና አስተሳሰብና ፍላጎቱ እስካለ ድረስ እንኳን ሁለት ሶስት ቋንቋ ይቅርና መቶም ሊያስተናግድ የሚችል ሰፊ ውቅያኖስ ነው።

በማያገባን የህዝብ የመብትና የማንነት ጉዳይ ውስጥ ገብተን፣ ይህንን አድርግ ያን አታድርግ ማለትና፣ ለአንድ ህዝብ ከራሱ በላይአስበውለትይህኛው ይሻልሃልና ያንን ተው፣ ይህንን እንጂ ያንን አታድርግ ማለት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የራስን መብትና የሥራ ድርሻ አለማወቅ ይመስለኛል። ኦሮሚኛ ተጨማሪ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ቢሆን እንኳን ማህበረሰብ ይቅርና አንድም ግለሰብ አይጎዳም። ዋናው ነገርእንዳይሆን መታገልወይምአለመከልከልነው። የተከለከለ ነገር ደግሞ አጓጊ ስለሆነ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ያንን የተከለከለን ነገር ለማግኘት ህግን እንኳ ጥሶም ቢሆን ሊያገኘው ይሞክራልና። ስለዚህ፣ ጊዜውን ጠብቆ መፈጸሙ ላይቀር፣ ዛሬ ኦሮሚኛን ተጨማሪ የፌዴራሉ የመሥርያ ቋንቋ ማድረግ ሁሉንም የሚጠቅም ነውና ሰንካላ ምክንያት ማቅረቡን ትተን የሚተገበርበትን አቅጣጫ ተባብረን በመቀየሱ ላይ እንረባረብ።

**** ጄኔቫ፣ 8 th March 2018

wakwoya2016@gmail.com

 

 

                                                              Copyright ©2008 GPO/OPC Allrights Reserved